ውድ ኤልማኒያ፡

እኔና ታላቅ እህቴ ስናድድግ ከኛ ቤት ውስጥ እብሮን የሚኖር ዘምድ አይጠፋም ነበር። ከእነዚህም ዘመዶቻችን መካከል የአባታችን ታናሽ ወንድምና የአባቴ የአክስቱ ልጅ ይገኙበታል። እኔና እህቴ የእባቴን ወድንድም እንደታላቅ ወንድማችን ነበር የምናየው። በመካከል እናታችንና አባታችን ይፋቱና እኔ፣ አባቴ፣ አጎቴና የአባቴ የአክስቱ ልጅ አብረን መኖር ጀመርን። ትዝ ይለኛል አባቴ በወር ቢያንስ ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ለሥራ ወደ ክፍለሃገር ስለሚወጣ እኔ፣ አጎቴና የአባቴ አክስት ልጅ  አብረን እንሆን ነበር። የአባቴ የአክስቱ ልጅ የአንደኛ አመት የዩኒቨርስት ተማሪ ነበረች። እኔ ደግሞ ገና የስድስተኛ ዓመት ተማሪ። አጎቴ፣ እኛ ቤት ያደገው የአባቴ ውንድም ደግሞ ዩኒቨርስቲ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ ዓመትም አልሆነውም። የአባቴ የአክስቱ ልጅ ማለተም የአጎቴም የአክስቱ ልጅ ከአጎቴ ጋር የሆነ የሆነ ነገር የሚያደርጉ መሰለኝ አባቴ ለሥራ ክፍለሃገር በሚወጣባቸው ሳምንቶች። ታዲያ በነዚህ በአንደኛው ማት አባቴ በሌለበት ምሽት ማለት ነው አጎቴ ከእንቅልፌ ይቀሰቅሰኛና “ለምን ሦስታችንም አብረን በትልቁ አልጋ ላይ አንተኛም” ይለኝና በጊዜው ያልጠበኩትን ነገር በማድረግ በገዛ አባቴ አልጋ በልጅነቴ አስገድዶ ደፈረኝ። ከዚያች ለሊት ጀምሮ ሕይወቴ ሕይወትም አልሆነ። በትንሽነቴ ገና ሃይስኩል ሳልገባ በድብቅ ማጨስ፣ መጠጣት ጀመርኩኝ። ካየኝም ወንድ ጋር ሁሉ መባለግን ሥራዬ አደረግኩት። ምንም እንኳ በትምሕርቴ የተሳካልኝ ከዚያም አሁን ደግሞ ብዙዎች የሚቀኑበት ዓይነት ሥራና “ኑሮ” ቢኖረኝም እራሴን እንደቆሻሻ ሰው ነው የማየው። ከዚያም ባለፈ የማየው ወንድ ሁሉ የሚፈልገኝ ከእኔ ጋር ለመቅበጥ ብቻ እንደሆነ ስለማስብ ለቁም ነገር እንኳ ለሚፈልጉኝ ልቤን መክፈት አልፈልግም። ምን ትለኛለህ?

ወ/ሪት ሥም የለሽ ስለጥያቄሽ በእጅጉ ልትደነቂ ይገባል። ነገር ግን ጥያቄሽን ለመመለስ ከመሞከሬ በፊት አንድ ነገር ማስተካከል እፈልጋለሁ። አንቺ ሥም የለሽ ብለሽ ነው እራስሽን ያስተዋወቅሽው። እኔ ደግሞ ሥም ያለሽ እያልኩኝ ነው ምላሼን ለመስጠት የምሞክረው።  ምን መሰለሽ ወ/ሪት ሥም ያለሽ፣ ግለሰቦች ገና በለጋነታቸው እድሜ ሥነ-ልቦናዊና ወሲባዊ ተኮር በሆነ አሰቃቂ ጥልቅ ስብራት ውስጥ ሲያልፉ አንድ የሚነጠቁት ዓቢይ የሕይወታቸው መርሆ ቢኖር ስለራሳቸው ያላቸውን ክቡር አመለካከት ማጣት ነው። በለጋ እድሜ ባሉ ልጆች ላይ የአካል፣ የሥነ-ልቦናና ወስባዊ ጥቃት (Adverse Childhood Experiences (ACEs) የሚያደርሱ አከአናብስት የጨከኑ ግለሰቦች የሚሰርቁት የነዚህን ልጆች ክብረ-ንጽህና ብቻ ሳይሆን የነዚህን ሕጻናት ስብዕናና በራስ መተማመን ጭምርም ነው። ስለሆነም የተደፈረው ክብርሽ ብቻ ሳይሆን ማንነትሽ፣ የማንነትሽ መታወቂያ የሆነው ሥምሽም ነው። ከዚህ ለዓመታት ከምትማቂቅበት ስሜታዊና ማኅበረሰባዊ ጥልመት ለመወጣት ወደሚያስችለው ጉዞ ለመግባት ቆርጠሽ ተነስተሽ ከሆነ፣  ይሄንን የእድሳት ጉዞ የተሰረቀውን ሥምሽን ከማስመለስ መጀመር ይኖርብሻል።

ይህንን ያህል ስለሥምሽ ካልኩኝ፣ በጥያቄሽ ዙሪያ የሚነሱ ጥቂት ዓበይት ምልከታዎችን አብረን እንቃኝ። በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን ጥያቄ ለመጠየቅ አስበሽ፣  ከዚያም ሃሳብሽን ሳትቀይሪ መጻፍ መቻልሽ ቀላል ድል እንዳልሆነ ላስገነዝብሽ እወዳላሁ። አሁን ባለሽበት ቦታ ሆነሽ ታላቅ ድርጊት እንዳከናወንሽ እንድታውቂ እፈልጋለሁ። ይህን ማስታወሺያ መጻፍ ላንቺ ቀላል ድርጊት እንዳልነበረ ማሰብ እጅግ አዳጋች አይደለም። ምክንያቱም እያንዳንዷ በማስታወሺያሽ ላይ ያሰፈርሺያቸው ፊደላት ያችን የመከራ ሌት ያስታዉሱሻልና። እንዳንቺ በመሳሰሉ በልጅነት ስሜታዊና አካላዊ ስቃይ የደረሰባቸው ግለሰቦች የደረሰባቸውን አሰቃቂ መከራ በውስጣቸው እንደቋጠሩ ለወዲያኛው የሚያልፉበት አንደኛው ምክንያት ስለደረሰባቸው መከራ መጻፍ ወይንም መናገር አይደለም ማሰብ አይፈልጉምና ነው። ለምን ቢባል? በግዳጅ የደረሰባቸውን፣ ከአቅማቸው ቁጥጥር ውጭ በሆነ መንግድ የወረደባቸውን አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ባሰቡ ወይንም ስለጉዳዩ በጻፉ አለበለዚያም በተናገሩ ቆጥር ያንን አሰቃቂ ደቂቃ፣ ሰዓት እየደጋገሙ ስለሚኖሩት ነው።

በአንቺ ላይ የደረሰው ጥቃት ሲታሰብ እንዴት ይህን የመሰለ አሰቃቂ ተግባር በቤተሰ መካከል ሊሆን ይችላል የሚሉ አይጠፉም። እውነታው ግን አሳዛኝ ሃቅ ነው። ከገዛ ቤተሰብ በሚደርስባቸው አካላዊና ወስባዊ ጥቃት የሚማቅቁ እምቦቃቅላዎች ብዙዎች ናቸው። በተጨማሪም፣ በአብዛኛው የአስግድዶ መድፈረንና የመሳሰሉትን አሰቃቂ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃትን በሕጻናት እንዲሁም ባልደረሱና በደረሱ ልጃገረዶች ላይ የሚያንደርሱት የቤተሰብ አባላት አለበለዚያም በቤተሰቡ ዘንድ ዕምነት የተጣለባቸው ቤተዘመዶች ወይንም የወላጆች ጓደኞች ይሆናሉ። አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ከዚህ ጋር የሚነሳው ዕውነታ ደግሞ፣ በዚህና በተለያየ መንገድ ሰቆቃቸውን የሚያሰሙን እህቶቻችን አንዳንዴም ወንዶሞቻችን ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ነው። ይህ እንዴት ይሆናል ለሚሉ መልሱ።

            1ኛ፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ባሉ ሃገራት በአንድ በተጣበበ የመኖሪያ ቤት ውስጥ አንቺ እነደነገርሽን ሁሉ ከቤተሰብ ጋር የሚኖሩ፣ አንዳንዴም ከልጆች ጋር የሚያድጉ ቤተዘመዶች ብዙ ናቸው። በዚህ በተጣበበና በተጨናነቀ የመኖሪያ ቤት ውስጥ አልጋ መጋራት ወይንም መሬትም ላይ ከሆነ የሚተኛው አብሮ መተኛት የተለመደ ነው። ከዚሁም በተጨማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን አብረው ከሚኖሩ ቤተዘመዶች ሊደርስ ከሚደርስ ወስባዊ ትንኮሳና አስገዶ መድፈር ልጆቻቸውን ከአደጋ መከለከል እንደሚገባቸው አይዞርላቸውም። ከገጠር የመጣን ዘመድ ወይንም አብሮ የሚያድግን የራስን ወንድም አለዚያም እህት በማመን (የልጆቹን አክሥት/አጎት) ለጋ ወይንም የደረሱ ልጆቻቸውን ከነዚህ በተዘመዶች ጋር በመተው ለቀናትና ለሳምንታት በቤት የማይገኙበት ሁኔታ ይኖራል። የተጠጋ ዘመድ ወይንም አብሮ የሚያድግ አጎት ወይንም አክስት ሁሉ ልጆችን አባላጊ ነው ማለት እንዳልሆነ እያስረገጥኩ፣ ነገር ግን በአንድ የተጣበበ ማንም ከማንም ራስን ለመጠበቅ ወይንም ለመሸፈን በማይቻልበት ቤት ውስጥ ከቤተዘመድ፣ ከወላጆች ጓደኞች ጋር አብረው የሚያድጉ ልጆች ለጥቃት አልፈው የሚሰጡበት  ሁኔታ እንግዳ ነገር አለመሆኑን ለማስረዳት እፈልጋለሁ።

            2ኛ፡ የአንቺን ማስታወሺያ ልዩ ከሚያደርጉት ሌላው ነጥብ አንዱ ደግሞ ከጥቃቱ ጋር የወስቢ ተጠቂዎች የሚደርሳቸው ማስጠንቀቂያ ነው። “ከእኔ ጋር ያለሽን ይህንን ወስባዊ ግኑኝነት ለወለጆች ትነግሪና ወይንም ትናገርና ወላጆችሽን/ወላጆችህን እግድላለሁ ወይንም እንቺን/አንተን ክፉኛ እጎዳለሁ” የሚሉት ማስፈራራቻዎችና ማስጠንቀቂያዎች ተጠቂዎቹ መከራቸውን በውስጣቸው ቋጥረው በየዕለቱ እንዲሞቱ ያስገድዳቸዋል። አንዳንዴም “እስዋ ናት ያሳሳተችኝ፣ አለዚያም የምትይውን/የምትለውን ሁሉ እክዳለሁ” በማለት ለሁልጊዜ ተጠቂዎችን ይሸቡቧቸዋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ በቤተሰብ መካከል የጠብ መንሥኤ ላለመሆን በማለት ተጠቂዎቹ የውስጣቸውን እሳት በሆዳቸው እንዳዳፈኑት ለመዝለቅ ይሞክራሉ። “አንድ ነገር ትንፍሽ እንዳትዬ፣  ካረግሽ ግን ቤተዘመዱ ሁሉ ነው በዚህ ጉዳይ የሚታመሰው” የሚለው ማስፈራሪያና ከአጢቂዎቹ የሚመጣ ዛቻ የጥቃት አድራሾቹ አንዱ አፍ የመለጎሚያ ዘዴያቸው ነው።

            3ኛ፡ ተጠቂዎች ራሳቸው “ብናገርም ማንም አያምነኝም፣ እኔኑ ነው የሚቆጡኛና የሚያሙኝ” በማለት ሥቃያቸውን እንደተሸከሙ ጎብጠው ይቀራሉ። ሌሎቹ ደግሞ “እኔን ጥፋተኛ ቢያደርጉኝሽ? ለምን ይህንን ልብስ ሲጀመር ለብስሽ? የሆነ ነገር አድርገሽ/አድርገህ ነው አጎትሽን/አክስትህን እዚህ ሃሳብ ውስጥ የከተትሺው/የከተትከው” እባላለሁ በማለት ዝምታውን ይመርጡታል።   

ከተጠቀሱት ውስጥ በየትኛው ምክንያት ታስረሽ እንደ ከረምሽ ባላውቅም፣ ከተጠቀሱት አንዱ ወይንም ሁለቱ አለዚያም ሦስቱ የሥቃይሽን ዘመን እንዳስረዘሙብሽ መገመት ከባድ አይደለም። ለአንቺ ያለኝ ቃል፣ የደረሰብሽ ጥቃት ከአንቺ የተነሳ አይደለም። በምንም ዓይነት ሁኔታ ስለደረሰብሽ መደፈር ምንም ሃላፊነት መውሰድ የለብሽም። ሃላፊነት መውሰድ ካለብሽ፣ ከአሁን በኋላ ስለምትወስኚው የሕይወት አቅጣጫ መሆን አለበት። እንቺ በደረሰብሽ ተመሳሳይ ወስባዊ ጥቃት የሚያልፉ ልጆች ሁለት ዋልታዊ ወስባዊ ልምምድ ውስጥ እንደሚገቡ ይታወቃል። አንዳንዶቹ ከደረሰባቸው ጥቃት የተነሳ ወስባዊ ግኑኘንትን የሚጠየፉና የሚጠሉ ይሆናሉ። ሌሎቹ ደግሞ ምን አልባትም እንዳንቺ ያለልክ በወስባዊ መረብ ይጠመዳሉ። እነዚህ ምንም እንኳ ካያቸው ግለሰብ ሁሉ ጋራ ለመባለግ ወደ ኋላ የሚሉ ባይሆንም ነገር ግን የወስቢን ለዛ የማጣጣም ፍልጎቱም አቅሙም የላቸውም። ካዩት ጋር የሚተኙት ስለራሳቸው ያላቸው ክብር ስለወደቀ፣  አንዳንዴም በሌላው ላይ ያላቸውን የወሲብ የበላይነት ለማሳየት ካላቸው ውስጣዊ ሕማም የተነሳ ነው።

ምን ትለኛለህ? ላልሺኝ መልሱ፣ ተስፋ አለ፣ እርዳት ማግኘት ትቺያለሽ፣ ራስሽን በመውደድ በትክክል ለሚወድሽም ልብሽን ለመክፈት ትበቂያለሽ፣ ብቻሽን የመሰቃየቱ ዘመን ሊያከትም ይችላል ነው።  ወደ ብርሃን ለመውጣት፣ ከሚደጋገሙ አሰቃቂ የሌለት ሕልሞች ለመንቃት፣ ነጻነትን ለማግኘት የምትጓዢበት ጉዞ ሂደትን ይጠይቃል። ይህም ሂደት አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበረሰባዊና መንፈሳዊ ንጠረ-ነገሮችን የሚያካትት ነው። ስለሆነም በሜሪላንድ አከባቢ ያሉ በኪሊኒካል ሳይኮሎጂ ሙያ የተሰማሩ ባለሙዎች አሉና እርዳታ የመፈለጉን ስልክ መደወል ጀምሪ። ስትፍልጊ ግን አንቺን በመሰል በልጅነት እድሜ በደረሱ ሰቆቃዎች ዙሪያ ተጨማር ስልጠና የወሰዱ ባላሙያዎች (Trauma and PTSD focused clinical intervetion) አጠያይቂ። የ Psychology Today (psychlogytoday.com) ድረገጽ የሥነልቦና ባለሙያዎችን ለማግኘት ፍልጋሺን ለመጀመር ጥሩ ቦታ ነው። የምትችይውን ያህል ሞክሪና፣  በቅርብ የሚሆን ቀጠሮ የሚሰጥሽ ባለሙያ ካጣሽ አስታዊቅኝ በማፈላለጉ በኩል እንድረዳሽ።

ቸር ይግጠመን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Post comment