በገዛ እጅዎ እራስዎን ከማጥፋትዎ በፊት ያንብቡኝ
-በኢልማንኒያ-
እንደ አውሮጲያዊያኑ አቆጣጠር በ1985 ራሱን ለመግደል ሲሰናዳ አቶ ኬን ባልድዌን ገና ሃያ ስምንት አመቱ ነበር። ዓመታትን ያስቆጠረው ከድባቴ ጋር ሲያደርግ የነበረው የዕለት ከዕለት የጨለማ ውስጥ ፍልሚያ ልቡን ማሳሳት ብቻ ሳይሆን ተስፋውን አስቆርጦታል። ተኝቶ ሲነቃ ደስ አይለውም። “ለምን ነቃሁ? ለምን እንደተኛሁ በዚያው ለሁል ጊዜው አላሸለብኩም?” በሚሉት ጥያቄዎች እራሱን ይኮንናል። ለአቶ ኬን ባልድዌን ሕይወት እርባና፣ ትርጉም፣ ጣዕም የሌላት እሥር ቤቱ ናት። ኑሮ የማያቋርጥ የሽቅብ ጉዞ ሆኖበት ይዳክራል። ምንም እንኳን በምሕንድስና ሥራ የተሰማራ፣ የምተወደው ሚስትና የሦሥት ዓመት ሴት ልጅ ብትኖረውም፣ የመኖር ፋይዳ ከእሳቤው ከጠፋ ሰንብቷል። በተቃራኒው ግን “እኔ ለቤተሰቤ ሸክም ነኝ። የእኔ ችግር መቋጪያ የለውም። ቤተሰቦቼ ከምኖር ይልቅ በሞቴ ይጠቀማሉ። ቢያንስ ቢያንስ ስለኔ አይጨነቁም” የሚሉት ድባቴ ካጨናገፈው አዕምሮ የሚፈልቁ የሽንፈት ምክሮች ምናቡን ገዝተውታል።
በነዚህና በመሳሰሉት እሳቤዎች ሲዘወር የከረመው የአቶ ኬን ባልድዌን አንጎል የራስን ሕይወት በራስ ማጥፋትን የግልግል መፍቴሕ አድርጎ አቀብሎታል። አቶ ኬንም በአውሮጲያዊያኑ ዘመን አቆጣጠ በ1985 በወረ-ነሃሴ በሃያኛው ቀን ከእንቅልፉ እንደነቃ ራሱን እንድሚያጠፋ ከራሱ ጋር ተማመለ። ከዚያም ባለቤቱንና ልጁን ለመጨረሺያ ጊዜ በመሰናበት “ዛሬ ዘግየት ብዬ ነው ከሥራ የምወጣውና እንዳታስቡ” ብሎ ራሱን ለመግደል ሁነኛ ቦታ ነው ብሎ ወደመረጠው በሳንፍራንሲስኮ ወደሚገኘው የወርቃማው ደጅ ድልድይ አቀና።
ወደ ድልድዩ አንደደረሰም የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ አቶ ኬን እንዲህ ይላል። “በድልድዩ ላይ እየተረማመድኩ ፍርሃት ፍርሃት ብሎኛል። በእጅጉም እንደምጎዳ ሳስብ ጨንቆኛል። ቢሆንም ግን በቃ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም። ካለሁበት ሰቆቃ ለማምለጥ እራሴን መግደል አለብኝ በማለት እራሴን አደፋፈርኩት።” ይህ ዓይነቱ በመጨረሺያ ደቂቃ ላይ የሚከሰት ማማመንታት በአብዛኛው እራሳቸውን ለመግደል ሙከራ ያደርጉና ከመሞት የተረፉ ግለሰቦች የሚያስምሩበት የሕይወት ተሞክሮ ነው። የዚህ ማስታወሺያ አንኳሩ ነጥብ ግን አቶ ኬን እግሮቹ የድልድዩን ወለል ለቀው ከ223 እግር እርዝመት ወደ ጠለቀው ውኃ በሰዓት 75 ማይልስ ፍጥነት ወደ ታች እያሽቆለቆለ የመከስከስን ሂደት ሲጀምር የዞረለት የሃሳብ ሽውታ ነው።
“ልክ እግሮቼ የድልድዩን ወለል ለቀው ወደ ቁልቁል ልደፈቅ አየሩ ላይ እንዳለሁ መሳሳቴ ተሰማኝ። መፍትሔ የላቸውም ያላኳቸው ችግሮቼ ሁል ቀላል እንደነበሩ ገባኝ። ራሴን ለማጠፋት መወሰኔና ራሴን ለመድፈቅ እርምጃ በመውሰዴ ተጸጸትኩኝ” በማለት እራሱን ከመግደል ሙከራው ተርፎ መግለጫ ሲስጥ ተደምጧል።
ከዚህ እውነተኛ ታሪክ በመነሳት ጥቂት ነጥቦች ራስን በራስ ስለመግደል ማንሳት ጠቃሚ ነው።
1ኛ፡ በድባቴ የሚጠቁ ሁሉ ራሳቸውን ይገድላሉ ማለት ባይቻልም፣ በአብዛኛው የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ግለሰቦች በድባቴ የሚጠቁ ናቸው።
2ኛ፡ ድባቴ ከመደበር ያለፈ የስነ-ልቦናና የአዕምሮ ጥቃት ነው። በአብዛኛው ሁኔታ በዚህ ሕመም የሚጠቁ ግለሰቦች ስለ ሦሥት ጉዳዮች ያላቸው ግንዛቤ ይንሸዋረርባቸዋል።
ሀ. ስለራሳቸው ያላቸው ግምት የተበላሸና የዘቀጠ ነው። “እኔ ዋጋ የለኝም። እኔ ተስፋ የለኝም” በሚሉና የራስን ማንነት በሚንዱ እሳቤዎች የተቀፈደዱ ናቸው። ራሳቸውን የሚኮኑኑ፣ ከሌሎች ጋር በመሆን ሕይወትን በደሥታ የማጣጣም ፍላጎትና አቅም የከዳቸው፣ የውስጥ መነሳሳታቸው የተሰለበባቸው ናቸው።
ለ. ስለ አከባቢያቸው ያላቸው ግንዛቤ የጨለመ ነው። ስለራሳቸው ያላቸው አናሳ ግምት ስለአከባቢያቸውም ያላቸውን እይታ ያጨልምባቸዋል ማለት ነው። “እኔ ብቻ ሳልሆን ያለሁበትም አከባቢ የተስፋ ጭላንጭል አይሰርጽበትም። የተከበብኩት እልባት በሌለው ውጥንቅጥ ውስጥ ነው። የተበላሸውና የተኮላሸው ነባራዊው ሁኔታ የእድሜ ይፍታህ ግዞት ቤቴ ነው” በሚሉትና በመሳሰሉት ምልከታ ያሉበትን ሁኔታ የሚቃኙ ናቸው። ከዚህም የተነሳ ራሳቸውን ከአከባቢያቸው ሁናቴ፣ ቤትሰብ፣ ማኅበረሰብ የሚያገሉ፣ ከልክ ባለፈ ብቸኝነት የሚታወቁ ናቸው።
ሐ. ስለ ወደፊቱ ምንም ዓይነት ተስፋ የማይታያቸው ናቸው። በድባቴ የሚሰቃዩ ግለሰቦች፣ ያሉበት ብቻ ሳይሆን የሚጨልማባቸው የወደፊቱም ብርሁነት የማይታያቸው ይሆናሉ። “የኔ ነገ ለኔ ብርሃን” ነው ብለው የሚቀኙ ሳይሆኑ “የኔ ነገ መከራ ነው። ነገን በጉጉት እንድጠብቅ የሚያነሳሳኝ ተስፋ የለኝም። ዛሬ የሆነው ነገም ይሆናል፣ እንደውም መከራዬ ይበዛል” በማለት ነገን በጉት ሳይሆን በተስፋ መቁረጥ የሚጠበበቁ፣ ከዚያም ባለፈ መሞትንና የሞትን ሃሳብ በእሳቤያቸው የሚያንገዋሉሉ ይሆናሉ።
3ኛ፡ የትኛውም የሕይወት ተግዳሮት የራስን ሕይወት አያስከፍልም። ድባቴ ባደመነው አንጎል የሚታሰብ ማንኛውም እሳቤ የመጨረሺያ ግብዓት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በድባቴ የተጠቁ ግለሰቦች በውስጣቸው የሚያብላሉት የነገውን ልማት ሳይሆን የሞትን ጥቃት ነው። በድባቴ በተመታ አንጎል የሚዘወር ስለ ራስ፣ ስለአከባቢ እንዲሁም ስለወደፊቱ የሚቀደድ ትልም መደምደሚያው እድገት ሳይሆን ሽንፈት ነው። ስለሆነም “እራስህን አጥፋ። ከዚህ ጨለማ ውስጥ መውጪያው አንድ ነው እርሱም እራስን መግደል ነው” የሚል ሃሳብ የሚመላልስብቸው ግለሰቦች በዚህ ሁኔታ እያሉ የማይታመነውን እራሳቸውን አምነው እራሳቸውን የመግደል ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት እርዳታ ማግኘት ይቻላልና 800-273-8255 በመደወል ባለሙያዎችን ያነጋግሩ። ከዚህም በተጨማሪ 911 በመደወል በራሳቸው ላይ ያላቸው በሕይወት የመኖር መተማመን እንደጎደለባቸው በመግለጽ ተገቢውን እርዳት በማግኘት እራሳቸውን በገዛ እጃቸው ከመግደል ያትርፉ። እርዳታ ማግኘት ይቻላልና እባክዎ የገዛ ሕይወትዎን በገዛ እጆዎ አያጥፉ።
እራስን በገዛ እጅ ከማጥፋት መከላከያ ስልክ ቁጥር፡ *****800-273-8255****