ከአዕምሮ እና ከሥነ-ልቦና ጋር የተያየዙ የጤና እክሎችን በሚለከት ግልፅነት የተሞላበት የመመካከርና የመነጋገር እጥረት አለ። ይህ እጥረት ደግሞ ገና በማደግ ላይ ናት የምትባለውን ኢትዮጲያን ብቻ የሚያጠቃ ተግታሮት ሳይሆን አደጉ የሚባሉ ሃገራትንም በሮች የሚያኳካ ሙሉ ተቀባይነትን ያላገኘ የከረመ እንግዳ ነው። የምዕራቡ ዓለም፣ የሰሜናዊቷን አሜሪካን ጨምሮ በሥነ-ልቦና ቀውስና በአዕምሮ መታወክ ዙሪያ የሚያንፀባርቀው ፈራ ተባና የውይይት ቁጥብነት በአብዛኛው የሚመነጨው ከአልሸነፊነት ሰባራ ወኔ ውስጥ ነው።

 

ይህ “እኔነትን” ላለማስደፈር ወይንም “ደካማ” መስሎ ላለመታየት ብሎም የጓዳን መከራ ለመሸፈን የሚደረግ የአደባባይ ፉከራ አያሌዎች የሚገባቸውን እርዳት በጊዜውና በብቃት እንዳያገኙ ሰንካላ ደንቅሮባቸዋል። ብዙሃኑ ምዕራባዊያን የሥነ-ልቦና እና የአምሮን ጥቃት፣ የዕፅ ሱሱኝናትንም ጨምሮ የሚቃኙት በራስ ገዝ መነፅር ውስጥ ነው። “ይሄ የእኔ ችግር ነው። እኔው እራሴው ለራሴው ችግር መፍትሔ አገኝለታለሁ። ማንም ሰው በአዕምሮ ሕመም፣ በሥነ-ልቦና ቀውስ እንዲሁም በሱስ ተገዢነት እንደምማቅቅ እንዲያውቅብኝ አልፈልግም” በማለት ሥልጡን የሆነውን ሕክምናና እርዳታ ከማግኘት እራሳቸውን ይገታሉ። ለነዚህ ምዕርብዊያን የእዕምሮ ሕመም፣ የሥነ-ልቦና ጥቃት፣ የዕፅ ሱሰኝነት የደካማነትና እራስን በአግባቡ ያለመግዛት ምልክቶች ስለሆኑ በግልፅነት ስለ ጥቃቶቹ ተነጋግሮ ተገቢውን መፍትሔ ለማግኘት ይቸገራሉ።

ለዚሁም በቂ ግንዛቤ ለማግኘት የእንግሊዟ ንግሥት የልጅ ልጅ ልዑል ሃሪ እና አሜሪካዊትዋ ባላቤቱ ሜጋን ማርከል ከኦፕራ ዊንፊሪ ጋራ በቅርቡ (March 2021) ያዳራረጉትን ዓለምን ያናጋገረ ቃላ መጠይቅ መከለስ ጠቃሚ ነው።  ከተላየየ ሚዲያ ዘርፎች፣ የዘውዱ ቤተሰቦችን ጨምሮ የደረሰባትን ዘር ተኮር ጥቃት ሜጋን ስትናገር፣ እንደ ጎርፍ  በላይዋ ላይ የደረሰባት የስብዕንና የማንነት ሰለባ አዕምሮዋንና ሥነ-ልቦናዋን ከመጉዳት አልፎ መኖርን እስከመጥላት እንዳደረሳት አመላክታለች። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ በራሳዋ ላይ ያላት መተማማን እየመነመነ በመሄዱ የገዛ የራሷን ሕይወት ለማጥፋት እንደማትመለስ እየገባት በመጣ ጊዜ ወደ በኪንጋሃም ቤተ መንግሥት የሰራተኞ ጉዳይ ጽህፈት ቤት በመሄድ የሥነ -ልቦናና የአዕምሮ ሕክምና ድጋፍ እንዲደረግላት እንደጠየቀች በጥያቄ እና መልሱ ላይ አስምራበታለች።

የተሰጣት የምላሽ “አይዞሽ! የሚያሰፈልግሽ ሁሉ እገዛ ይደረግልሻል” ሳይሆን “የሥነ-ልቦና ቀውስ ወይንም ከአዕምሮ ሕመም ጋር የተነካካ ማንኛውም ዜና የዘውዱን ቤተሰብ ሥምና ታሪክ ያጠልሻልና ልንረዳሽ አንችልም” ነበር። ሜጋን እንዳለችው፣ ተሰጠኝ ያለችው መልሥ አሳዛኝ ቢሆንም በሥነ-ልቦና እና በአዕምሮ ጥቃት ዙሪያ ለተሰማሩ ባለሙያዎች የሚያስደንቅ አልነበረም። ምክንያቱም ዛሬም ቢሆን ከምዕራቢያዊያኑ በአዕምሮ ሕመም እና የሥነ-ልቦና ጥቃት ዚሪያ ካላቸው ሰንካላ መረዳት ጥላ ሥር የተንሻፈፈ ምልክታ ስላለ ነው። ይህም ሸፋፋ ምልካታ የሚያጥንጥነው የአዕምሮ ሕመመ፣ የዕፅ ተገዢነትና የሥነልቦና ልሽቀት “የደካማነት” ምልክት ነው በሚለው ዛቢያ ላይ ነው። 

ከወደ ምድረ ኢትይዮጲያ በሥነ-ልቦና እና በአዕምሮ ጥቃት ዙሪያ የሚታየውና የሚሰማው መጭበርበር  ደግሞ መንፈሳዊነትን የተላበሰ ዓይነጥላ ነው። የሥነ ልቦናና የአዕምሮ ጥቃት ሰለባ የሆኑ አያሌ ዚጋዎች የሚጠቅማቸውን አስፈላጊ እርዳት ከማግኘት ይልቅ በደረሳባቸው ጥቃት ምክንያት ለጨከነ ስብዓዊና ማኅበራዊ ጥቃት ሲዳረጉ ይታያል። በአዕምሮ ሕመም የተጠቁ ሕሙማን በሰንሰለት እየተቀፈደዱ በጨለማ ጓዳ ውስጥ ይጣላሉ። የሰው ፊትና የፀሃይ ብርሃን እንኳን ለማየት ሳይታደሉ እዲሜአቸውን የሚቀጩትን ቤት ይቁጠረው። ከተደበቁበት ጨለማ አምልጠው ወደ ውጭ ወጥተው የተገኙ ቢኖሩ ደግሞ “እብድ!እብድ!እብድ!” በማለት የሰፈር ልጆች በድንጋይና በጩኸት የሚያሳድዱአቸውን የአዐምሮ እና የሥነ-ልቦና ሕሙማንን አላያሁም የሚል ኢቶዮጲያዊ አለ ለማለት ያዳግታል።

እንዚህንና የመሳሰሉት ቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ጥቃት ለምን በአዕምሮና በሥነ-ልቦና እክሎች በሚጠቁ ሕሙማን ላይ ይደርሳል ብሎ መጠየቅ ወደ ምንጩ ያመላክታል። ለምን ቢባል፣ የአዕምሮ እክልን በሚመለከት የአብዛኛው ኢትዮጲያዊ ግምትና እሳቤ ከእርግማን ጋር የተያየዘ ነው። የአዕምሮ ሕመም መንሥዔው ከመለኮታዊ ሂደት ጋር ይፈረጃል። ስለሆነም የታማሚው ቤተሰቦች ስለጥቃቱ ተነጋግሮ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ጭራሽ የታማሚውን መፈጠር ቢዘንጉት ይመርጡታል። የሕመተኛው ችግር በመላ ቤተሰቡ ማንነት ላይ የሚያጠላው አሉታዎ ጥላ እንዳለው ተደርጎ ስለሚታመን በአዕምሮ ሕመም የተጠቃ የቤተሰብ አካል እንዳለ እንኳ እውቅና ለመስጠት አይፈለግም። “በፈጣሪ የተቀሰፈ” ልጅ፣ ወንድም፣ ዘመድ አለኝ ብሎ ወደ አደባባይ ደፍሮ የሚወጣ ቤተ-ዘመድ ማን ነው? “ከተቀሰፈ” ግለሰብስ ጋር ማን ራሱን ያብራል? የአዕምሮ የታማሚው ጥቃት በቤተሰቡ ላይ የሚያንፀባርቀውና ሰለ ቤተሰቡ የሚገልጠው ያልተቀደሰ መንፈሳዊ ሚስጢር ያለ ይመስል የታማሚውን የጤና ማጣት መደበቅ ብቻ ሳይሆን ታማሚውን መደበቅ መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል።

“አምላክ የቀሰፈው” ብቻ ሳይሆን፣ የአዕምሮና የሥነ-ልቦና ቀውስ የደረሰበት ግለሰብ “ጋኔን የለከፈው” ተደርጎም ይታያል። ይኸኛው ምልከታ ደግሞ በአዕምሮ ህመመ የሚጠቁ ግልሰቦች ከቤተሰብ እንዲሁም ከሚኖሩበት ማኅበረስብ መካከል እንደ እርኩስ እንዲታዩ ከመዳርጉም ባሻገር በሥነ-ልቦና እና በአዕምሮ በሽታ የሚጠቁ ሕሙማን ትክክለኛውን እርዳታ እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። “ጋኔን ለለከፈው” ሰው መፍትሔው “አዋቂ ነው። ባለመድኃኒተኛ ነው” በማለት የተጨነቀ ቤተሰብ የጠንቋዮችን በመጋረጃ የተከለለ ፊት ደጅ በመጥናት ውድ ጊዜውንና ጥሪቱን ያሟጥጣል። ይህንን ቤተሰባዊ፣ ማኅበረሰባዊና ከዚያም ባለፈ ሀገራዊ በአዕምሮ ጤንነትና ሥነ-ልቦናዊ ሰለባ ዙሪያ የተጋረጠን ተግታሮት ለመቅረፈ ልብ የገዛና በምክንያታዊነት ላይ የተገነባ ንግግር አስፈላጊ ነው።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Post comment